ሃይማኖት የሚለው ቀጥተኛ ትርጉሙ እምነት ማለት ሲሆን ይኸውም የነገረ መለኮትን ትምህርት; የአምልኮትን ሥርዓት ከእምነትም የተነሣ የሰውን አካሄድ ያጠቃልላል 2ኛ ጢሞ 4:7:: በተጨማሪም ሃይማኖት ማለት እግዚአብሔርን አውቀን በእውነትና በትክክል መንገድ ተመርተን የምናመልክበት ነው ምክንያቱም በሃይማኖት ያለው መንገድ ፈጽሞ የማይለወጥና ፍጹም የሆነ የማያረጅ; የማይቀየር እና እንከን የሌለበት ዘለዓለማዊ እውነት መንገድ ነው:: ይህንንም ሃይማኖት ያስተማረን እርሱ የሚታዩትንና የማይታዩትን ፍጥረታትን በሙሉ ካለመኖር ወደ መኖር የፈጠረ ከመላእክት ከሊቃነ መላእክት ከአጋእዝትና ከሥልጣናት ከኪሩቤልም ከሱራፌልም በላይ የሚኖር: እርሱም
ከፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ የነበረ ከምስጋና ሁሉ በላይ ልዑል የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ነው:: አምላካችን ያስተማረን እውነተኛይቱ ሃይማኖት አንዲት ብቻ እርሷም ተዋሕዶ ናት ኤፌ 4:5:: ተዋሕዶ ስንል አምላክ የሰው የሆነበት ሰውም አምላክ የሆነበት ምስጢር የተከናወነበት የተፈጸመበት ነው:: ዮሐ 1: 1-14:: እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ያስተምረናልና ሲነግረንም ሲያስተምረንም የማይለወጠውን የማይሻረውን የሃይማኖት ፍሬ በሕይወታችን ይዘን እንድንሄድ የሚያስተምሩን; ከሃይማኖት ፈቀቅ እንዳንል የሚመክሩን አባቶችን በየዘመኑ እያስነሣ በሥነ ፍጥረት: በነቢያት: በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ: በመንፈስ ቅዱስና በቅዱሳት መጽሐፍት አስተምሮናል:: በሃይማኖት ከኖርን መላ ሰውነታችን ለእርሱ እናስገዛለን; እንቀደሳለን: ኑሮአችን በሙሉ ይባረካል:: " እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር እራሳችሁን ጠብቁ" ይሁ 1:20:: ይህ የሚያስረዳን የሚያስተምረን የሚያረጋግጥልን በተቀደሰ እውነት ውስጥ የመኖር ጥበብ የሚገኘው በሃይማኖት መሆኑን ብቻ ነው:: ለዚህም ነው ካህኑ በቅዳሴ ማርያም ላይ አቤቱ ሁሉን ለፈጠርክ; ለማትታይ አምላክ ለአንተ ሰውነታችንን እንዘረጋለን: ሁሉን ለምታዋርድ ለአንተ ራሳችንን እናዋርዳለን: ሁሉን ለምታሰግድ ለአንተ እንሰግዳለን: ሁሉን ለምትገዛ ለአንተ እንሰግዳለን ሲሉ ዲያቆኑ ደግሞ በፍርሃት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ስገዱ ይላል ሕዝቡም ተቀብሎ አቤቱ በፊትህ እንሰግዳለን እናመሰግንሃለንም ብለው ይሰግዳሉ:: በተቀደሰ እውነት አና ሕይወት ውስጥ በሃይማኖት መኖር ማለት በእንደዚህ አይነት መልኩ ሲኖር ብቻ ነው::
0 comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.