ኑ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ ኑ በፀሎት ወደአምላክ ቅረቡ ፤ በፀሎት ማለት እንዴት ነው? ይህስ የልባችሁን ምስጢር ሁሉ ሳትደብቁ እርሱ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልጋችሁ መናገር ማለት ነው ፤ እንዲህም በሉ ፦ “ጌታ ሆይ ወደ አንተ መምጣት እፈልጋለሁ ፡ ጌታ ሆይ ካንተ ተለይቼ እኔ ምንም ነኝ ፡ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴን አጣሁ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ደስታየን ሁሉ አጣሁ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴ ትርጉም አልባ ሆነ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴ ጣእም አልባ ሆነ” በሉ ፤ ዳግምም ከእግዚአብሄር እግር ስር ተደፍታችሁ እንዲህ በሉት፦ “ አምላኬ ሆይ ፦ ወደ አንተ መመለስ እፈልጋለሁ ፤ ነገር ግን ጠላቶቼ ከእኔ በእጅጉ የሚበልጡ ናቸው ፤ ነፍሴንም አምላክሽ አያድኑሽም የሚሏት ብዙ ናቸው” ፡፡
ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ “ ጌታ ሆይ ታደገኝ
ወደ አንተ የምመለስበትን መንገድ ምራኝ” በሉት ፤ ለአምላካችሁ ንገሩት ፦ “ካንተ ከተለየሁ ወዲህ አቅሜ ሁሉ ተዳክሟልና ጌታ ሆይ ልዩ ሃይልህን ላክልኝ ፡ ወዳንተ የምመለስበትን ልዩ ርዳታህን ስጠኝ ፤” በማለት፡፡ ብዙ ሰወች በመደጋገም “ወደ እግዚአብሄር የምመለሰው እንዴት ነው ?” ይላሉ፡፡ ከእግዚአብሄር እግር በታች ራሳችሁን ጣሉ ፡ እንዲህም በሉት ፦ “ ጌታ ሆይ ሳትባርከኝ አልለቅህም ፡ ወዳንተ አቅርበኝ ፡ ከልጆችህ እንደአንዱ አድርገኝ ፡ ሃጢአቴን ብቻ ይቅር እንድትልልኝ አልሻም ፡ ይልቁንም ከሃጢአት ፍቅር ትለየኝ ዘንድ ጭምር እንጂ ፡ ” በሉት ፦ ዳግምም “ ጌታ ሆይ የሃጢአት ፍቅር ልቤን ተቆጣጥሮታልና ይህን ካላስወገድኩ ወዳንተ መቅረብ አይቻለኝም ፡ ጌታ ሆይ የሃጢአትን ፍቅር ከልቤ ላይ ንቀል ፡” በሉት ዳግምም እንዲህ በሉት ፦ ”ጌታ ሆይ ከሃጢአቴ ነፅቼ ወዳንተ መምጣት እንደምን ይቻለኛል? ይልቁንስ መጀመሪያ አንተ ናልኝ ሃጢአቴንም ደምስስ እንጂ “ እንዲህም በሉት ፦ “ በራሴማ ሃጢአትን ማስወገድ ብችል ወዳንተ መቼ መመለስ ያቅተኝ ነበር? እኔ ግን አንተ ከሃጢአቴ እንድታርቀኝ እወዳለሁ ፡ ጌታ ሆይ ፦ ሃይልህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” በሉት፡፡
እመኑኝ የምወዳችሁ ልጆቼ ፦ ትክክለኛዋን ፀሎት ያወቃት እርሱ ትክክለኛዋንም ንስሃን የሚያውቅ እርሱ ነው ፤ ማር ይስሃቅ እንደተናገረው ፦ “ንስሃ
ከፀሎት ውጭ እንደሚገኝ የሚያስብ ሰው እርሱ በዲያቢሎስ የተታለለ ነው” ምክንያቱም በፀሎት ወደ እግዚአብሄር የምትመለሱበትን ሃይልን ታገኛላችሁና፡፡ ስለሆነም ከየትኛውም ስራ ይልቅ ራሳችሁን ለፀሎት አስገድዱ ፤ ምክንያቱም በፀሎት አማካኝነት በእናንተና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን ግድግዳ አስወግዳችሁ እንደገና ወደእርሱ ትመለሱ ዘንድ ይቻላችኅልና ፤ በጣም ብዙ ሰወች ከፀሎት ይልቅ ለአገልግሎት መትጋታቸው የሚገርም ነው ፡ ወይንም ከፀሎት ይልቅ በንባብ የሚተጉትም እንደዚያው ፡ ወይንም ከፀሎት ይልቅ በተመስጦ የሚተጉትም እንደዚያው ፡ ወይንም ከፀሎት ይልቅ በመንፈሳዊ ስብሰባወች ለመታደም የሚተጉትም እንደዚያው ፤ ለዚህ እኮ ነው ከእግዚአብሄር ጋር ባላቸው ግንኙነት የማይሳካላቸው ፤ ይፀልያሉ ፡ ያነባሉ ፡ ደግሞም ስብሰባወችን ይታደማሉ ፡ በዚህ ሁሉ ሰአት ከእግዚአብሄር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም ፤ ምንም አይነት ግንኙነት ፡፡
ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ ወደእግዚአብሄር ተመለሱና ከእርሱ ውሰዱ ፤ አንዳንድ ሰወች በመፀለይ ለእግዚአብሄር የሚሰጡት እንዳለ ያስባሉ ፡ ለእግዚአብሄር ቃላትን ይሰጡታል ፡ ጊዜን ፡ ምናልባትም ስሜታቸውን ፤ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ፀሎት ከእግዚአብሄር የመውሰድ ጉዳይ ነው ፤ እርሱ ሰጭ እንጂ ተቀባይ አይደለምና ፤ በፀሎቱ ስኬታማ ውጤትን የሚያመጣ ሰው እርሱ ከእግዚአብሄር ስለሚወስደው የፀለየና እንደዚያም የሚያምን ነው ፤ እርሱ ነው በፀሎቱ የተሳካለት፡፡ በምትፀልዩበት ጊዜ ከእግዚአብሄር ሃይልን እንደተቀበላችሁ ከተሰማችሁ ፡ ያን ጊዜ ውጤታማ ፀሎት ፀለያችሁ ፤ አንድ ሰው ፀልዮ ከእግዚአብሄር በረከት ከተቀበለ፡ እንግዲህ ይህ ሰው ነው ውጤታማ ፀሎት ያቀረበው ፤ ማንም በፀሎት በፀፀትና በንስሃ ወደእግዚአብሄር ቢቀርብ እርሱ ውጤታማ ፀሎትን አቀረበ ፤ አንድ ሰው ቢፀልይና ለቅድስና ቢታገል ፡ ይህ ሰው ፀሎቱ ውጤታማ ሆነ ፤ አንድ ሰው ቢፀልይና ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት ቢያጠናክር ይሄኔ ውጤታማ ፀሎትን አቀረበ፡፡
እግዚአብሄር እንድትመጡ ይናገራችኅል ፡ በፀሎት ኑ ና የሚያስፈልጋችሁን ልስጣችሁ እያለ ፤ ነገር ግን እናንተ ለሁለት ደቂቃ ብቻ ትፅልዩና ወዲያው ትሰለቻላችሁ ፡ ከእግዚአብሄርም አንዳች ሳትቀበሉ ትሄዳላችሁ ፤ እግዚአብሄር ወደእናንተ ያይና እንዲህ ይላል ፦ “ስለምን ከእኔ ሳትቀበሉ ተመለሳችሁ? የሚያስፈልጋችሁን ልሰጣችሁ ወድጄ ነበርና ፤ ስለምን ቶሎ ተመለሳችሁ ያዘጋጀሁላችሁን ሳትወስዱ?” እያለ ፤ ነገር ግን እናንተ ቶሎ ሰለቻችሁና ለመሄድ ወሰናችሁ ፤ እሺ ሂዱ ፡ ከዚያ ግን እግዚአብሄርን መፈለግ ትጀምራላችሁ አታገኙትም ፤ ጥላችሁ ስትሄዱ ያጣችሁት ምንም ሳትይዙ መሄዳችሁን ብቻ እንዳይመስላችሁ ፡ በልባችሁ ለእግዚአብሄር ጊዜ እንደሰጣችሁት ማሰባችሁም ጭምር እንጂ ፤ ወዲያውም ከመንፈሳዊ የስኬት ድርጊቶች ውስጥ መፀለያችሁን ትፅፋላችሁ፡፡
ይህ ግን ፀሎት አይደለም!!! ከእግዚአብሄር ከቶ ምን አገኛችሁ? እግዚአብሄርን አጥብቃችሁ ልትይዙት ይገባል ፡ አጥብቃችሁ ፡ መቼም ቢሆን ካንተ አልለይም ፡ መለየትም አልፈልግም ፡ ማለት አለባችሁ፡፡ ስለዚህ እኮ ነው ለፀሎት ትእግስት የሚያስፈልገው ፤ ያለትእግስት ከእግዚአብሄር አንዳች እንኳን ልትቀበሉ አትችሉም ፤ በፀሎታችሁ ትእግስተኞች ልትሆኑ ይገባችኅል ፤ እግዚአብሄርን ንገሩት ፦ ከእግርህ በታች እንደሆንኩ እቆያለሁ ፡ በረከትህንም ሳትሰጠኝ አልነቃነቅም ፡ ከእግዚአብሄር በረከትን ካልተቀበልኩ እርሱን መያዜን አልለቅም ፡ ካልባረከኝ አልለቅህም ፡ እይዘዋለሁ ወዴትም ይሄድ ዘንድ አልተወውም ፤ እንግዲህ ይህ ነው በፀሎት ውስጥ ያለው ትግል ፤ ሰወች ፀሎት እንዴት እንደሚፀለይ አልተማሩም ፡ እነርሱ የሚያስቡት ፀሎት ማለት ጥቂት ቃላትን መናገር ይመስላቸዋል ፡ አይደለም፡፡
ፀሎትን አዘውትሩ ፡ ከእግዚአብሄርም አንዳች እስክትቀበሉ ድረስ ታገሉ ፤ አንዳች እንኳን ካልወሰዳችሁ ሳትቀበሉ የትም እንደማትሄዱ ንገሩት ፡ ፀሎቴን አልገታም በሉት ፡ እንደተፃፈ አንተ ሩህሩህ መሃሪ አምላክ ነህ ፡ የለመነውን ሁሉ
የምትሰጥ ነህና እንግዲህ እኔም ለምኜሃለሁ እስከምትሰጠኝ ድረስ ወዴትም አልሄድም በሉት ፤ በፀሎታችሁ ከእግዚአብሄር ጋር ታገሉ ፡ ያን ጊዜ ታርፋላችሁ ፡ በፍቅር ትሞላላችሁ ፡ በፀሎታችሁም ብርቱ ትሆናላችሁ ፡ ከንቱ ነገርንም መደጋገም ትተዋላችሁ ፡ እንዲያውም ልባችሁን በእግዚአብሄር ፊት ትዘረጋላችሁ ፤ የሳሙኤል እናት ሃና በፀሎቷ ጊዜ ታለቅስ ነበር ፡ በልቧም ልጅ እንደምታገኝ ቃል ሳይገባላት ከቤተመቅደሱ ላለመውጣት ወስና ነበር ፤ ንጉስ ዳዊት ከእግዚአብሄር በረከትን እስኪቀበል ድረስ ፀሎቱን አላቋረጠም ፡ በመጀመሪያ “ጌታ ሆይ ፦ አስጨናቂወቼ ምንኛ በዙ” በማለት ፀለየ ፤ ቀጥሎም እንዲህ አለ ፦ “ እናንተ ክፉ አድራጊወች ከእኔ ራቁ ፡ እግዚአብሄር ፀሎቴን ሰምቶልኛልና ፡ ጌታየ የልመናየን ድምፅ አድምጧልና ፡ ጌታየ ፀሎቴን ሰምቷልና“፡፡ ኑ ወደእግዚአብሄር ተመለሱ፡፡
0 comments:
Post a Comment
Note: Only a member of this blog may post a comment.